WHAT'S NEW AT ALERT CSH

news image

Dec 17, 2023

ከ200 በላይ ለሚሆኑ የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር አባላት ነፃ የህክምና አገልግሎት ተሰጠ፡፡
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ የህክምና ባለሙያዎችን ይዞ ከመደበኛው የህክምና አገልግሎት በተጨማሪ በተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት የሚሰጠውን ተከታታይ የሆነ ነፃ የበጎ አድራጎት የህክምና አገልግሎቱን ቀጥሎበታል፡፡ ሆስፒታሉ ነፃ የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ የበጎ አድራጎት ህክምና ቡድን በማቋቋም ለተለያዩ የማህበረሰብ አካላት እየሰጠ በሚገኘው የመልካምነት ስራ ላይ ከፊደራል ሆስፒታሎች በቀዳሚነት ደረጃ ላይ እያስቀመጠውም ይገኛል፡፡ ለዚህም የተለያዩ የምስጋና እና የእውቅና ምስክር ወረቀቶች እየተበረከተለት ነው፡፡ የህክምና ቡድኑ በዛሬው እለት ከ7 ሺ በላይ የማህበረሰብ አካላት በሚኖሩበት መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ነፃ የህክምና አገልግሎት የሰጠ ሲሆን በቆዳ ህክምና፣በዓይን ህክምና፣በአጥንት ህክምና ፣በውስጥ ደዌ ህክምና እና በነርብ ህክምና ላይ ችግር ያለባቸውን አረጋውያን ማህበረሰቦችን ማገልገል ተችሏል፡፡ ነፃ የህክምና አገልግሎት የበጎ አድራጎት ስራው በሆስፒታሉ ህክምና ቡድን ከመደበኛ የህክምና አገልግሎቱ በተጨማሪ ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው በሚለው መርህ ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራም የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች ገልፀዋል፡፡
more
news image

Dec 14, 2023

ሆስፒታሉ በተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት መጎብኘቱን ቀጥሏል፡፡
ታህሳስ 4/2016 ዓ.ም የፊደራል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሰራተኞች የአንጋፋውን አለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተለያዩ የህክምና አገልግሎት መስጫ ክፍሎችን ተዘዋውረው በመጎብኘት ታካሚዎችን ጠይቀዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሽመልስ ገዛኸኝ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ለእንግዶች ያስተላለፉ ሲሆን በመልዕክታቸው ሆስፒታሉ ከ34 ሄክታር መሬት በላይ ያረፈና ከዘጠኝ አስርት አመታት በላይ ያስቆጠረ ታሪካዊ የህክምና ማዕከል እንደሆነ ገለፃ አድርገዋል፡፡
በዚህም ሆስፒታሉ በምርምር፣ አለማቀፍና ሃገር አቀፍ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም የሆስፒታል አገልግሎት ስራዎችን አንጋፋ በሆኑ የህክምና ባለሙያዎች ለተገልጋዩ ማህበረሰብ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝና ሆስፒታሉን ከሌሎች ሆስፒታሎች በተለየ መልኩ ከስጋዊ ህክምና በተጨማሪ መንፈሳዊ ህክምናዎችን በማጠናከር የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ታካሚዎችን ጉብኝት ማድረጋቸውና ለህሙማኑም ሆነ ለባለሙያዎች የስራ ተነሳሽነትን እና ብርታትን የፈጠረላቸው መሆኑን ጠቁመው ታካሚን መጠየቅ ክብር በመሆኑ እናንተም አክብራችሁን ስለመጣችሁ ምስጋና ይገባችኋል ሲሉ ዋና ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
በእለቱ ዋርድ 4፣ የስነ- አዕምሮ ህክምናና ምርምር አገልግሎት ክፍል፣መድሃኒቱን የተለማመደ ቲቢ ህክምና ክፍል፣የጥርስ፣የመንጋጋ፣የአፍና የፊት ቀዶ ጥገና ህክምና ክፍሎችን ጨምሮ ሆስፒታሉ የህክምና ቱሪዝም ለማድረግ በቅርስነት ያስመዘገበውን የመጀመሪያውን ሆስፒታል ጉብኝት ተደርጎባቸዋል፡፡
በተመሳሳይ የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩትን አዲሱን ህንፃ የጎበኙ ሲሆኑ የምርምር ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የአለርት ሆስፒታል መፈጠር በአፍሪካ በአይነቱ የመጀመሪያና የተለየ የምርምር ማዕከል እንዲመሰረት አድርጓል፡፡ ለዚህም አለርት ሆስፒታል ቀደምትና ብዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ ያለና በተለያዩ ሃገር አቀፍና አለምአቀፍ ተቋማት ዘንድ እውቅናው እየጨመረ መሄዱን ገልፀዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ ከተገኙት አቶ ደስታው ብዙአየሁ የፊደራል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የቢሮ ሃላፊ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት የሆስፒታሉን ታካሚዎች መጠየቃችን ተቋሙን የበለጠ ያወቅንበትና ብዙ ልምዶችን ያገኘንበት በመሆኑ በሌሎች ሆስፒታሎችም በተመሳሳይ ደረጃ እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል፡፡
ወ/ሪት አዳነች በዳዳ ሌላኛዋ አስተያይት ሰጪ ሲሆኑ እንደ ሃገር ሆስፒታሉ እየሰጠው ያለው አገልግሎት የሚበረታታ ነው፡፡ የተቋማችን ሰራተኞች ታካሚዎችን በመጠየቃችን እየተሰጠ ያለውን ህክምና አገልግሎት ከሚጠበቀው በላይ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ሆስፒታሉ አገልግሎት የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ለጎብኝዎች፣ለታካሚዎችና ለሰራተኞችም ጭምር መንፈሳቸውን የሚያድሱበት ለእይታ ውብና ማራኪ የሆነ ነፋሻማ ተቋም መሆኑም አስደስቶናል ሲሉ አስተያይታቸውን ሰጠዋል፡፡
more
news image

Dec 14, 2023

የጃፓን አለማቀፍ ትብብር ድርጅትና የካይዘን የልዕቀት ማዕከል ከተለያዩ የፊደራል ሆስፒታሎች ጋር በመሆን የሆስፒታሉን የካይዘን አተገባበር ጉብኝት አድርገዋል፡፡ 
ታህሳስ3/2016 ዓ.ም የጃፓኑ አለማቀፍ ትብብር ድርጅት ከካይዘን የልዕቀት ማዕከል ጋር በጋር በመሆን በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተሰራውን የካይዘን ትግበራ ተግባረዊ በሆነባቸው የሆስፒታሉ የስራ ክፍሎች፣ከጤና ሚኒስቴር ሜዲካል ሰርቪስ፣ከየካቲት 12 ሆስፒታልና ከቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከተገኙ እንግዶች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱና በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የሆስፒታሉ የጤና መረጃ ስርዓት ዳይሬክቶሬት አቶ ሃብታሙ ብርሃኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ሆስፒታሉ የካይዘን ትግበራውን በመጀመሩ በከፍተኛ ሁኔታ ለውጥ ያመጣበትና የማሻሻያ ስራዎችን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ትግበራው በተለያዩ የስራ ክፍሎች ተጠሪ ባለሙያ ተመድቦለት ስራው ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የካይዘን ትግበራው ተግባራዊ ከሆነባቸው የስራ ክፍሎች መካከል ደግሞ የህሙማን የመረጃ ክፍል፣የፋርማሴ አገልግሎትና ባዮሜዲካል ወርክ ሾፕ ክፍል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ካይዘን ለሆስፒታላችን እንደሲስተም በመተግበሩ ለተገልጋዩ ማህበረሰብ የሚታዩ ለውጦችን እያሳየ በመሆኑና የካይዘን አንዱ መግቢያችን የሆነውን የተገልጋዮችን የአገልግሎት መስጫ ቦታዎችን በትክክል ተግባራዊ በመደረጋቸው ሶስቱንም ካይዘን ተግባረዊ የሆነባቸውን ክፍሎች በጉልበትም ይሁን በገንዘብ የሚወጣውን ወጪ ማዳን መቻሉን አመስግነው በተጀመሩ የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች ላይ ማስፋፋቱን የምንቀጥል ይሆናል ሲሉም ለእንግዶች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሆስፒታሉ ያለበትን የካይዘን የአፈፃፅም ደረጃና በተመረጡ የሆስፒታሉ ካይዘን ትግበራ በሚደረግባቸው የስራ ክፍሎችም የእውቅናና የምስክር ወረቀት ከጃፓን አለም አቀፍ ትብብርና ከካይዘን የልዕቀት ማዕከል የተሰጣቸው መሆኑንም ወ/ሮ የልፍኝ አማረ በሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርት ላይ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን አለርት ሆስፒታል የካይዘን ትግበራውን አዋጭና ቀጣይነት ያለው መሆኑን ተረድቶ ተግባራዊ በተደረገባቸው የስራ ክፍሎችም ሆስፒታሉ ለውጥ ያመጣበትና ለሌሎች የፊደራልና የክልል ሆስፒታሎችም እንደልምድ የሚወሰድ ተቋም መሆኑን ከጤና ሚኒስቴር የሜዲካል ሰርቪስ መሪ ስራ አስፈፃሚ ክፍል በእለቱ የተገኙት ሲ/ር እታፈራሁ አላማው ገልፀዋል፡፡
ሆስፒታሉ በቅርብ ጊዜ የተሰጠውን የካይዘን ትግበራ እየተጠቀመበትና ለውጥ እያመጣበት ለሌሎችም ተቋማት ተሞክሮ ሆኖ ስለተገኘ እኛም ከሆስፒታሉ ጎን በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ የሚደግፉ መሆኑንም የጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ድርጅትና የካይዘን የልዕቀት ማዕከል ተወካዮች የገለፁ ሲሆን ካይዘን ተግባረዊ የሆነባቸውን የስራ ክፍሎችን ተዘዋውረው ጉብኝት አድርገዋል፡፡
more
news image

Dec 13, 2023

ሆስፒታሉ በተለያዩ የመንግስትና የግል ድርጅቶች የሚሰጠውን ነፃ የበጎ አድራጎት የስራ እንቅስቃሴ መስራቱን ቀጥሏል፡፡
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ታህሳስ 2/2016 ዓ.ም በውድ አረጋውያን በጎ አድራጎት ማህበር በመገኘት በሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የሆስፒታሉን የህክምና ቡድን በመያዝ ከ100 በላይ የአረጋውያን ማህበር አባላትን ነፃ ህክምና አገልግሎት ሰጠዋል፡፡
በእለቱ አለም አቀፍ የአረጋውያንና የፆታዊ ጥቃት ቀንን ምክንያት በማድረግ ሆስፒታሉ የድፎ ዳቦና የውሃ ስጦታዎችን ያደረገ ሲሆን አለርት ሆስፒታል ከውድ አረጋውያን ማህበር ጎን በመቆም እስካሁን ላደረገውና እያደረገ ላለው የበጎ አድራጎት ስራ ከማህበሩ የምስጋና እና የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶለታል፡፡
የበጎ አድራጎት የእንቅስቃሴ ስራዎች ከመደበኛ ስራዎች በተጨማሪ ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
more
news image

Dec 9, 2023

ሆስፒታሉ ከኢትዮጵያ ቀዶ ህክምና ማህበር ፕሬዘዳንትና ኮሴክሳ ከፍተኛ የክርስታልና የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበረከተለት፡፡ 
በኢትዮጵያ ካሉ አንጋፋ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ የሆነው አለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በዓለም አቀፍ ለ23ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ከአስርት አመታት በኋላ ለ2ኛ ጊዜ የተከበረውን ከ14 የአፍሪካ ሃገራት በላይ መስራት የሚያስችለውን አለም አቀፍ የቀዶ ህክምና የብቃት ማረጋገጫ /ኮሴክሳ /The callege of surgeons of East, central, and southern Africa(COSECSA) ፈተና በጥሩና በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ስካይላይት ሆቴል በተካሄደው 23ኛው የኮሴክሳ አለም አቀፍ ሳይንትፊክ ኮንፍረንስ የኮሴክሳ ሰርጅን ኮሌጅ ያዘጋጀውን ፈተና ወስደው ያለፉ ከ 152 በላይ የተለያዩ ሰርጅን ባለሙያዎች ምርቃት ተከናውኖላቸዋል።
ይህንን አለም ዓቀፍ ፈተና እና ኮንፈረንስ የተሳካ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከተው አለርት ሆስፒታል የክርስታልና የእውቅና ምስጋና ምስክር ወረቀት ከኢትዮጵያ ቀዶ ህክምና ማህበር ፕሬዘዳንት የተበረከተለት ሲሆን ሆስፒታሉ በተለያዩ ጊዜያት በሚያከናውናቸው አለም አቀፍና ሃገር ዓቀፍ ዝግጅቶች ላይ ምስጋናዎች እየተቸሩት ይገኛል፡፡
more
news image

Dec 7, 2023

 የኮሴክሳ ሳይትፊክ ኮንፍረንስ በዛሬው እለት በስካይላይት ሆቴል አዲስ አበባ
23ኛው የኮሴክሳ ሳይትፊክ ኮንፍረንስ በዛሬው እለት በስካይላይት  ሆቴል አዲስ አበባ  የተጀመረ ሲሆን  ከኮንፍራንሱ በፊት ባለፉት ሁለት ቀናት የኮሴክሳ ሰርጅን ኮሌጅ ያዘጋጀውን ፈተና ወስደው ያለፉ 152  የተለያዩ ሰርጀን ባለሙያዎች ምርቃት ተከናውኗል።
በምርቃቱ ላይም የትምህርት ሚኒስቴር ምንስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ ያላችሁ በማለት የደስታ መግለጫ መልእክት ያስተላለፋ ሲሆን አክለውም የሰርጀሪ ሙያ ክቡር የሆነ የሰውን ልጅ ላይ የሚካሄድ  የነፍስ አድን ሙያ በመሆኑ ለሙያው ከፍተኛ ክብር ይገባዋል ሲሉ ገልፀዋል።
የኮሴክሳ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር በቅድሚያ ለተመራቂዎቹ እንኳን ደስ ያላችሁ በማለክት የመልካም ምኞታቸውን መልእክት ያስተላለፉ እና እንዲሁም ለዚህ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሆስፒታሎች እና ሌሎችንም ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል
more
news image

Dec 7, 2023

በሆስፒታሉ ሲሰጥ የነበረው አለም አቀፍ የቀዶ ህክምና የብቃት ማረጋገጫ /ኮሴክሳ /ፈተና ተጠናቀቀ፡፡ 
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በአለምአቀፍ ደረጃ ለ23ኛ ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ ደግሞ ከአስር አመታት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘውን አለምአቀፉን የቀዶ ህክምና የብቃት ማረጋገጫ/ኮሴክሳ/ፈተና እንዲያስተናግድ በሃገር አቀፍ ደረጃ ተመርጧል፡፡
ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው የቀዶ ህክምና የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ከ14 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የህክምና ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን በዚህ ፈተና ላይ በጠቅላላ ቀዶ ህክምና 100 ፈታኞችና 60 ተፈታኞች፣በአጥንት ቀዶ ህክምና 57 ፈታኞችና 43 ተፈታኞች እንዲሁም ከፕላስቲክና ሪኮንስትራክቲቭ ሰርጀሪ 17 ተፈታኝ እና 29 ፈታኞች በጥቅሉ ከ120 በላይ ተፈታኞች ተገኝተውበታል፡፡
በፈተናው ላይ የምስራቅ፣ የደቡብና የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ተሳታፊዎች በመሆን ከሁሉም አህጉራት የተውጣጡ ከ186 በላይ ፈታኝ ፕሮፌሰሮች በፈታኝነት የተገኙ ሲሆን ከ50 በላይ እንግዳ ተቀባዮችና አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተሳትፈውበታል፡፡
ይህ አለም ዓቀፍ ፈተና በተቋሙ በሚሰጥበት ጊዜ ለሆስፒታሉም ሆነ ለባለሙያው ትልቅ ልምድና ተሞክሮ የሚሆን ነው፡፡
ከተለያዩ ፈታኞችና ተፈታኞች ለሆስፒታሉ በተሰጠው ግብረ መልስ መሰረት ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለና ለወደፊትም ለሌሎች ሃገራትም የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ሆስፒታል እንደሚሆንም አስተያይታቸውን ሰጠዋል፡፡
በሆስፒታሉ የተካሄደው አለማቀፍ ፈተና በጥሩና በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ በመሆኑ ለዚህ ፕሮግራም ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ሆስፒታሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
more
news image

Dec 7, 2023

የሆስፒታሉን የመሰረተ ልማት የስራ አፈፃፅም የተከበሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጉብኝት አደረጉ፡፡
ህዳር 24/2016 ዓ/ም የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላትና የጤና ሚኒስቴር ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰን ጨምሮ የተለያዩ ሚኒስቴር ዴኤታዎች ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በተቋሙ እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ-ልማትና ሆስፒታል አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክቶችን አፈፃፅምና የህሙማን አገልግሎት አሰጣጥን ተዘዋውረው ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝቱ ላይ በአዲስ የተደራጁ የድንገተኛ አደጋና የጥርስ ህክምና ክፍል ጨምሮ በሆስፒታሉ ለታካሚ ምቹ የሆኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች የተጎበኙ ሲሆን ጉብኝቱ ለተቋሙ ሰራተኞች ተነሳሽነትን የሚፈጥርና በሚሰጡ ግብረ መልሶችም የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደሚያስችል ተገልጿል።
በጉብኝቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶና እና ሌሎች የምክር ቤት አባላትም ተገኝተውበታል።
more
news image

Dec 7, 2023

የሆስፒታል ቱሪዝም መስህብነትን ለመጨመር በጎ ተጽእኖ የሚኖረው የኮሴክሳ አለማቀፍ ፈተና በነገው እለት ይጀመራል፡፡
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አለማቀፍና ሃገር ዓቀፍ ግንኙነቶችን በማጠናከር ታላላቅ ክንውኖችን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
በሆስፒታላችን የፊታችን ሰኞ ሁለት ዋና ዋና አለማቀፍና ሃገር ዓቀፍ ዝግጅቶች የሚከናወኑ ሲሆን የመጀመሪያው በ14 የአፍሪካ ሀገራት መስራት የሚያስችል የቀዶ ህክምና የብቃት ማረጋገጫ /ኮሴክሳ /ፈተና ይሰጣል፡፡
የቀዶ ህክምና የብቃት ማረጋገጫ ፈተናው ከ14 የአፍሪካ ሀገራት ለተውጣጡ ከ170 በላይ የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጥ ሲሆን በዚህ ፈተና ላይ የምስራቅ፣ የደቡብና የመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡
በሚሰጠው ፈተና ከሁሉም አህጉራት የተውጣጡ ከ300 በላይ ፕሮፌሰሮች በፈታኝነት ይገኛሉ። ይህ አለም ዓቀፍ ዝግጅት መከናወኑ ሆስፒታሉን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን የእንቅስቃሴ ተግባር ውጤታማ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ የፊደራል ሆስፒታል የስራ እንቅስቃሴዎች በኤግዚቪሽን ለታይታ ይቀርባሉ፡፡
በተጨማሪም በእለቱ ከ200 በላይ የተከበሩ የተወካዮች ምክርቤት አባላት በተቋሙ እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ-ልማትና ሆስፒታል አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክቶችን አፈፃፅምና የህሙማን አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ጉብኝት ያደርጋሉ።
እነዚህ ታላላቅ ሁነቶች በሆስፒታሉ መከናወናቸው ለተቋሙም ሆነ እንደ ሃገር ለጤና አገልግሎቱ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።
የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከዘጠኝ አስርት አመታት በላይ ለተገልጋዩ ማህበረሰብ አንጋፋና አንቱ በተባሉ ህክምና ባለሙያዎች አገልግሎቱን እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታታሪና ብቁ አመራሮችን ይዞ አለም ዓቀፍና ሃገራቀፍ ግንኙነቶችን እያሰፋና እያጠናከረ ቀጥሏል፡፡
more
news image

Dec 7, 2023

ሆስፒታሉ ምቹ፣ውብና ጽዱ የህክምና አካባቢን የመፍጠር እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ህዳር23/2016 ዓ/ም የሆስፒታሉ ማኔጅመንት አባላት፣የተለያዩ የስራ ክፍል ሃላፊዎችና ሰራተኞች ማራኪ የህክምና ቦታን የመፍጠር የፅዳት ዘመቻዎችን አከናውነዋል፡፡
በዚህ የጽዳት ዘመቻ ላይ ለተሳተፉ አመራሮች፣የስራ ክፍል ሃላፊዎችና ሰራተኞችን የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ሽመልስ ገዛኸኝ ምስጋና አቅርበው በቀጣይ ሆስፒታሉን ጽዱና ማራኪ የህክምና ቦታዎችን የመፍጠር እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡
more

Contact Info

  1. +251 113 48 60 51 (Chief Executive Direcor)
  2. +251 113 47 16 32 (Chief Clinical Director)
  3. +251 113 48 11 63 (Chief Academic Director)
  4. hospital@alertcsh.org
  5. Zenebework, Kolfe Keranyo Addis Ababa, Ethiopia

Find Us On

  • Copyright © 2023 Alert Comprehensive Specialized Hospital. All Right Reserved