
🎉 እንኳን ደስ አልዎት!
የአራት አስርተ ዓመታት የቅንነት፣ የትጋትና የሙያ አገልግሎት ጉዞ – አቶ ፍቅሬ መኩሪያ
የኦኮፔሽናል ቴራፒ(Occupational Therapist) ፈር ቀዳጅ
ጅማሮ፦ ከፈተና ወደ ስኬት
አቶ ፍቅሬ መኩሪያ በ1958 ዓ.ም. ተወለዱ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ጠመንጃ ያዥ እና ስብስቴ ነጋሲ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ወቅት በነበረው የፖለቲካ ሁኔታና ብሔራዊ ውትድርና ምክንያት ትምህርታቸውን ለተወሰነ ጊዜ ለማቋረጥ ቢገደዱም፣ ያ ፈተና ለወደፊት ስኬታቸው መሠረት ሆኖ ቀረ።
በ1978 ዓ.ም. ከዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል በጤና ረዳትነት (Health Assistant) ተመርቀው በዚያው ዓመት አለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ተቀላቀሉ።
የዕድገት ምዕራፍ፦ ቋንቋ እንደ ድልድይ
በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቆዩበት ጊዜ በኦፕሬሽን፣ በተመላላሽ ክሊኒክ እና በፊልድ አገልግሎቶች ላይ በትጋት አገልግለዋል።
አማርኛ፣ ኦሮምኛ እና እንግሊዝኛን በብቃት የመናገር ችሎታቸው የሆስፒታሉን አመራር ትኩረት ስቦ ለውጭ አገር ባለሙያዎች ተርጓሚ ሆነው እንዲሠሩ አስችሏቸዋል። ይህም ወደ ሥራ ተኮር ሕክምና (Occupational Therapy) ዘርፍ የገቡበትን መንገድ ከፈተላቸው።
በ1980 ዓ.ም. በማታ ትምህርት 12ኛ ክፍልን በማጠናቀቅ ለቀጣይ የሙያ እድገታቸው ራሳቸውን አዘጋጁ።
ወደ ኬንያ እና ወደ ሙያ መሪነት
በ1982 ዓ.ም. በOccupational Therapy ዘርፍ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችን ለማሰልጠን በተሰጠው የነፃ ትምህርት ዕድል ተመርጠው ወደ ኬንያ ሄዱ። በ1985 ዓ.ም. ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ፣ በወቅቱ በጀርመን ባለሙያዎች የሚመራውን የOccupational Therapy ክፍል በኃላፊነት ተረክበው በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እንዲመራ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በሙያው እድገት ላይ ካበረከቷቸው ዋና ዋና አስተዋጽኦዎች መካከል፦
• በ1986 ዓ.ም. በዘርፉ የመጀመሪያውን የማስተማሪያ መመሪያ (Handout) ማዘጋጀት፣
• በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የOccupational Therapy ትምህርት እንዲጀመርና ዲፓርትመንቱ እንዲቋቋም ግንባር ቀደም ሚና መጫወት፣
• በ2004 ዓ.ም. በጤና መኮንንነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የClinical Working Group አባል ሆነው ማገልገል ይገኙበታል።
ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስከበሩ
አቶ ፍቅሬ በአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃም የታወቁ ባለሙያ ናቸው። የአፍሪካ የOccupational Therapy ክልላዊ ቡድንን በመወከል በዩጋንዳ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በታንዛኒያ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ተሳትፈዋል።
የግል ህይወት እና የአገልግሎት ትውፊት
አቶ ፍቅሬ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ናቸው። ለ39 ዓመታት በቆየው የሙያ አገልግሎታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች የአካል ብቃታቸውን መልሰው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
“አለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለተሃድሶ (Rehabilitation) ሕክምና እድገት ትልቅ ዕድል የሰጠ ተቋም በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል።” ይላሉ አቶ ፍቅሬ።
ዛሬም በሁለት የጤና ሙያዎች በተለያዩ ክፍሎች በንቃት እያገለገሉ በመሆናቸው፣ ለሆስፒታላችን፣ ለሙያቸው እና ለሀገራቸው ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ከልብ እናመሰግናቸዋለን።
እንኳን ደስ አለዎት አቶ ፍቅሬ መኩሪያ!
የእርስዎ ትጋት፣ ታማኝነት እና የሙያ ቁርጠኝነት ለትውልድ የሚተላለፍ አርአያ ነው። በቀጣይም ጤና፣ ሰላም እና የበለጠ ስኬት እየተመኘንልዎ ለሰጡት እና እየሰጡ ላሉት ክቡር አገልግሎት ከልብ እናመሰግናለን።